Ethiotelecom Logo

አርቲፊሻል ኢንተሊጀንስ


አርቲፊሻል ኢንተሊጀንስ

          አሁን 21ኛዉ ክፍለዘመን የቴክኖሎጂ ዘመን ነዉ፡፡ በዚህ ዘመን ነገሮች በዝግመታዊ ሳይሆን በቅፅበታዊ ለዉጥ ላይ ናቸዉ፡፡ አሁን ላይ ወደድንም ጠላንም እዉነታዉ የቴክኖሎጂ ጥገኛ ከሆንን ሰነባብተናል፡፡ በትንሹ እንኳን ፌስቡክ ሳንገባ ፣ ጎግል ሳንጎግል አንዉልም፡፡

          እስከ ቅርብ ጊዜያት ለዓለም አስፈሪ የነበረዉ የኒኩለር አለበለዚያም የተለያዩ ጁምላ ጨራሽ መሳሪያዎች ነበር አሁን ግን አስፈሪዉ እና ቢሊዮን ዶላሮችን እያንቀሳቀሰ የሚገኘዉ ይህ ሳይሆን ያለምንም መሳሪያ በጭንቅላታችን እና በኮምፒዉተሮችችን የምንገጥመዉ የሳይበር ጦርነት እና የአርቲፊሻል ኢንተሊጀንስ እሽቅድምድሞሽ ነዉ፡፡

          በእንግሊዘኛዉ አጠራር አርቲፊሻል ኢንተሊጀንስ (Artificial Intelligence) እየተባለ የሚጠራዉ የሳይንስ እና የቴክኖሎጂ ዘርፍ የ5ተኛዉ ትዉልድ የኮምፒዉተር መገለጫ ባህሪ ሲሆን አላማዉም ኮምፒወተሮች ልክ እንደ ሰዉ ልጆች የማገናዘብ እና ድርጊቶችን የመከወን ችሎታ እንዲኖራቸዉ ማድረግ ነዉ፡፡

          ኮምፒዉተሮች ብዙ መረጃዎችን በመስጠት እንዲማሩ ይደረጋል ፤ በአስገራሚ ሁኔታ ለሰዉ ልጆች ለመለየት እና ለማታወስ እጅግ አዳጋች የሆኑ ነገሮችን ኮምፒዉተሮች ከሰዉ ልጆች ጋር በማይነፃፀር ሁኔታ ያለምንም ስህተት ሲለዩ እያየን ነዉ፡፡

          አርቲፊሻል ኢንተሊጀንስ ከተለያዩ ቴክኖሎጂዎች ጋር በመጣመር ለአለም የተለያዩ ጥቅሞችን የሚሰጡ ዉጤቶች አሉት፡፡ የተነሳበት ዋና ዓላማዉም የሰዉ ልጆችን ሂወት ቀላል እና ምቹ ማድረግ ነዉ፡፡ ነገር ግን መድሀኒት እንኳን ሲዉጡት የጎንዮሽ ጉዳት እንዳለዉ ሁሉ አርቲፊሻል ኢንተሊጀንስ ጎዳቱ ቀላል አይደለም እያሉ የሚከራከሩ ወገኖችም አሉ፡፡

 

 

የአርቲፊሻል ኢንተሊጀንስ ጥቅሞች (ዉጤቶች) ተብለዉ ከሚነሱት መካከል

  1. የሰዉ ልጅ እንኳን ሊከዉናቸዉ ቀርቶ ከቶ ሊያስባቸዉ የማይችሉ ረጅም ጊዜ የሚፈጁ ስራዎችን ያቀላጥፋሉ፡፡
  2. ለግብርና እና ለምርምር ሳይቀር ከአየር ላይ ዉሀን ማመንጨት የሚችሉ ስራዎችን ሳይቀር እየከወነ ነዉ፡፡
  3. ሴንሰር ያላቸዉ ያለ ምንም አሽከርካሪ የሚከንፉ ተሽከርካሪዎች ፡፡ በየጉራንጉሩ ገብተዉ ግዳጅ ፈፅመዉ የሚመለሱ ሰዉ አልባ አዉሮፕላኖች ፣ የተለያዩ እጅግ ብዙ እና ዉስብስብ ምስሎችን የሚለዩ ማሽኖች ፣ ከኮምፒዉተር ጋር በተፈጥሮአዊ ቋንቋ መግባባት የሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎች ፣ የሰዎችን የእጅ ፅሁፍ ፣ ምስል እና ድሞፆችን በቀላሉ መለየት የሚችሉ ኮፒዉተሮች ፣ ሰዉ ፈፅሞ ሊደርስበት የማይችለዉ ቦታ ሁሉ እየገቡ ምስል ይዘዉ የሚወጡ ድሮኖች እና ጌሞች ይገኙበታል ፡፡
  4. ብዙ ቋንቋዎችን መተርጎም መቻሉ፡፡ በአለም ላይ ያሉ ቋንቋዎችን ወደ ፈለግነዉ ቋንቋ የሚቀይርን ጎግል፡፡
  5. ዋትሰን (IBM) - በካንሰር ምርምር ላይ ሳይቀር በጤና ላይ እና ብዙ ነገሮች ላይ ከፍተኛ ጥቅም የሚሰጥ፡፡
  6. ሶፊያ - ኢትጲያዉያን የተሳተፉበት እንደ ሰዎች መረዳት ብሎም የፊት እንቅስቃሴ መስጠት የምትችል ፤ የሳዉዲ ዜግነት ያገኘች የመጀመሪያዋ ግዑዝ አካል፡፡
  7. ካፕቻ(CAPTCHA) - ኮምፒዎተሮች ከሮቦቶች የሚደርስባቸዉን ጥቃት የደህንነት ጥቃት ለመከላል የሚያገለግል፡፡
  8. ፅሁፍን ወደ ንግግር መለወጥ የሚያስችል (Text to Speech)
  9. የፈለግንበትን መረጃ መፈለጊያ (Google Search Engine)
  10. ጎግል ካርታ (Google Maps) በአለም ላይ የፈለገንን ቦታ በቅፅበት ባለንበት ሆነን የምናይበት
  11. የምንወደዉን ሙዚቃ እየገመተ የሚያመጣልን ዩ -ትዩብ
  12. የተለያዩ መስፈርቶችን በመጠቀም ልናዉቃቸዉ የምንችላቸዉን ሰዎች የሚያመጣልን ፌስቡክ
  13. አርቲፊሻል ኢንተሊጀንስ በአንዳንድ መመዘኛዎች ከሰዎችም እጅግ ልቆ ይገኛል፡፡ ለምሳሌ - ሰዎች ለመከወን የሚከብዳቸዉን ስራ በቀላሉ መከወኑ ፣ ጊዜ ቆጣቢነቱ ፣ አስተማማኝነቱ ፣ ያለምንም እረፍት እና ተጨማሪ ወጪ ስራዎችን መከወን መቻሉ ፣ ሰዎች ሊደርሱባቸዉ የማይችሉ ቦታዎች ስራዎችን መከወኑ ፣ የተሰጠዉን ትዕዛዝ ያለ ስህተት መከወን መቻሉ ፡፡

 

 

የአርቲፊሻል ኢንተሊጀንስ ጉዳቶች ተብለዉ ከሚነሱት መካከል

  1. አርቲፊሻል ኢንተሊጀንስ ከፍተኛ ወጪ እና እዉቀት ስለሚጠይቅ ድሀዎችን ያገላል ተብሎ ይወቀሳል፡፡
  2. ብዙ ዉሃ ባያነሳም የሰዉ ልጅ በተፈጥሮ የተሰጠዉን ፀጋ ለአንድ ግዑዝ አካል መስጠት ከተፈጥሮ ጋር የሚቃረን ነዉ የሚል ሀሳብ ያስነሳሉ፡፡
  3. ኮምፒዉተሮች ፕሮግራም ከተደረጉት ዉጪ እንደ ሰዉ ልጅ ነባረዊ ሁነቶችን በብልሀት ማገናዘብ እና መከወን ይሣናቸዋል ፡፡
  4. የሰዉ ልጅ አስፈላጊነት ላይ ጥያቄ ምልክት ያስቀምጣል - ማለትም የሰዉ ልጆችን ከስራ ገበታ ያፈናቅላል ፤ ከጥቂት ጊዜ በኋላ እንደ አሜሪካ ያሉ ሀገራት ምናልባትም ቴክኖሎጂ የሰዉ ሀይላቸዉን ከተካላቸዉ የሰዉ ልጅ ሰርቶ የመኖር ህልዉና አደጋ ሊጋረጥበት ይችላል፡፡
  5. የሀይል ሚዛን እንዲያጋድል ያደርጋል፡፡
  6. ምናልባትም ለጦር መሳሪያነት ከተጠቀምንበት ካየናቸዉ ነገሮች ይበልጥ እጅግ አዉዳሚ ሊሆን ይችላል የሚሉ ይገኙበታል፡፡

          በተለያየ አጋጣሚዎች ስለ አርቲፊሻል ኢንተሊጀንስ ግንዛቤዉ ያላቸዉ ወይንም በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ በዚህ ዙሪያ የሚሰሩ ሰዎችን አግኝቼ ነበር፡፡ እስኪ የ 2ቱን ሀሳብ ለማስቀመጥ ልሞክር ፡-

          ዶክተር አያልነሽ በለጠ መኖሪያዋን በአሜሪካ ያደረገች በ LAC + USC Medical Center Los Angeles , California ክሊኒካል ፋርማሲስት ስትሆን በ University of South California ደግሞ በረዳት ፕሮፌሰርነት ሙያ የምትሰራ ትዉልደ ኢትዮጵያዊት ናት፡፡ ምንም እንኳን በስራዋ እና በአገልግሎቷ አንቱ ብትባለም እኔ ካለኝ አክብሮት እና ቅርበት አንፃር ሁሌ እንደምላት አንቺ ብዬ ልቀጥል፡፡ ዶ/ር ደቦ የእርዳታ ድርጅት የሚባል ግብረ ሰናይ ተቋም ከአጋሮቿ ጋር አቋቁማ ለሀገሯ ልጆች ነፃ የትምህርት እድል ፤ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ድጋፍ ከዚም በተጨማሪ እጅግ ሰፊ የማህበረሰብ አቀፍ ስራዎችን ትሰራለች፡፡

          ዶ/ር አያልነሽ ከሰራቻቸዉ ስራዎች አንዱ በሆነዉ ደቦ የትምህርት ማዕከል ዉስጥ አርቲፊሻል ኢንተሊጀንስ በተለይም ሮቦቲክስ ላይ ትኩረት አድርጋ የሮቦቲክስ ማዕከል በከፍተኛ ወጪ አቋቁማ ታዳጊ ተማሪዎች ያለምንም ክፍያ በነፃ ከልጅነታቸዉ ጀምሮ ከቴክኖሎጂዉ ጋር አብረዉ እንዲያድጉ እያደረገች ትገኛለች፡፡ እኔም በተደጋጋሚ ተገኝቼ እንዳየሁት በዚህ ቤት ዉስጥ ብዙ ተስፋ ያላቸዉ ገና 7ኛ እና 8ኛ የክፍል ደረጃ ያላቸዉ ህፃናት እጅግ ብዙ ፈጠራዎችን ሲከዉኑ ፣ ራሳቸዉን ቻይና እና አሜሪካ ብለዉ ከፍለዉ በቴክኖሎጂ ሲሽቀዳደሙ እና ሲፎካከሩ ፤ የዲዛይን ስርቆት እርስ በእርሳቸዉ እንዳይደረግባቸዉ ሲጠነቀቁ ፣ ባስ ሲልም ተሰረቅን ብለዉ ማስረጃቸዉን ሲያቀርቡ ፣ የዓለምን እዉነት በአንድ ቤት ዉስጥ ሲከዉኑ አይቻለሁ እንደዚህም አለ ብዬ ለራሴ ተደንቄያለሁ፡፡ በዚህ ቤት ዉስጥ በአስገራሚ ሁኔታ በዩኒቨርሲቲ ደረጃ የአርቲፊሻል ኢንተሊጀንስ ተማሪዎች ጭምር በተቋማቱ የማያገኙዋቸዉን በስያሜ ብቻ የሚያዉቋቸዉ መሳሪያዎች እና ቴክኖሎጂዎች እነዚህ ህፃናት ገና በለጋነታቸዉ ጠንቅቀዉ አዉቀዉ ይባስ ብለዉ አሻሽለዉ ሰርተዉባቸዋል፡፡

          ለዶ/ር አያልነሽ ይሄን የሮቦቲክስ ማዕከል ለማቋቋም ምን እንዳነሳሳት ለጠየኳት ጥያቄ የሰጠችኝ ምላሸም ፤ ይህ ቴክኖሎጂ ዓለምን በቅፅበት እየለወጠ የሚገኝ ቴክኖሎጂ ቢሆንም እንኳን ሀገራችን እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ሀገራት ግን የግንዛቤዉ ደረጃ ገና ስለሆነ ይሄንንም ክፍተት በመሙላት ወደፊት የሚመጡ ታዳጊ ህፃናት በዘርፉ የተሻለ ክህሎት ይዘዉ እንዲያድጉ እና የተሻለ ነገር በመፍጠር ተዕፅኖ እንዲፈጥሩ ለማስቻል በማሰብ እንደሆነ አስረድታኛለች፡፡ በምትኖርበት በሀገረ አሜሪካ ባለችበት የህክምና ሙያ ዉስጥ እንኳን ሳይቀር የአርቲፊሻል ኢንተሊጅንስ ሮቦቶች እጅግ ከባድ እና ጥንቃቄ የሚጠይቁ ህክምናዎችን ሳይቀር ከሰዎች በላቀ መልኩ እንደሚከዉን አብራርታልኛለች፡፡

          በመጨረሻ ዶክተር አያልነሽ ሶፍያን የሚያክል አለምን የሚያስደንቅ ትልቅ ስራ ላይ ኢትዮጲዉያን አመርቂ ዉጤት ማስገኘታቸዉ በሀገሪቷ ያለዉን የዘርፉን መነቃቃት የሚያሳይ እንደሆነ እሷንም እጅግ እንዳስደሰታት እና የበለጠ ተስፋ እንድታደርግ እንዳደረጋት ገልፃልኛለች ፡፡

 

          ዶክተር ትምኒት ገብሩ ባለ ብሩህ አዕምሮ ወጣት ስትሆን ገና በዚህ በወጣትነት ጊዜዋ እንደ አፕል እና ማይክሮሶፍት ያሉ የዓለም ቁንጮ የሆኑ ካምፓኒዎች መስራት የቻለች አሁንም በማይክሮሶፍት በአርቲፊሻል ኢንተሊጀንስ ሪሰርቸርነት እሰራች ያለች የአርቲፊሻል ኢንተሊጀንስ ቴክኖሎጂስት ናት፡፡ ዶክተር ትምኒትም ልክ እንደ ዶክተር አያልነሽ ሁሉ ለሀገሯ የተለያዩ ስራዎችን ትሰራለች ከነዚህም ዉስጥ ኢትዮጵያዉያን ሴቶች ቴክኖሎጂ ፈጣሪ እንዲሆኑ የምትሰራበት እና እንደ ዶክተር ጄላኒ ኔልስን ( ኢትዮ-አሜሪካዊ ወጣቱ የሀርቫርድ ተባባሪ ፕሮፊሰር ኮምፒዉተር ሳይንቲስት) ካሉ ኢትዮጵያዉያን እና የሌሎች ሀገራት ዜጎች ጋር በመሆን የሚሰሩበት አዲስ ኮደር ፕሮግራም ይገኝበታል፡፡

          ይቺን ለኢትዮጵያዉያን የዘመኑ ምሳሌ የሆነች ቴክኖሎጂስት የማግኘት እድል ገጥሞኝ ነበር፡፡ ዶክተር ትምኒት አርቲፊሻል ኢንተሊጀንስ ለዓለም እጅግ ብዙ ቱሩፋቶችን እንደሚያበረክት ታስረዳለች ነገር ግን ጥቁሮች በተለይ አፍሪካዉያን ከዚህ ቴክኖሎጂ ጋር እኩል መራመድ አለመቻላቸዉ ስጋት እንሚፈጥርባት ትናገራለች፡፡ የእኛ ከአለም ጋር እኩል አለመጓዝ እንደ አሜሪካ እና ሌሎች የአለም ታላላቅ ሀገራት በሌሎች ሀገራት ላይ ከፍተኛ ተዕፅኖ እንዲኖራቸዉ ያስችላቸዋል በማለት ፍርሀቷን ታንፀባርቃለች፡፡ እሷም ይሄንን በማሰብ ለሀገሯ የቻለችዉን አስተዋፅኦ ለማበርከት ቀና ደፋ እያለች ትገኛለች፡፡

          አሁን ላይ ማሽኖች እንደ ሰዉ ማሰብ ጀምረዋል ፡፡ በፍጥነት በመከወን ፤ ብዙ መረጃ በመሸከም እና ነገሮችን ያለ ስህተት በመለየት ደግሞ እንዲያዉም ከሰዉ ልጆች የበለጠ ርቀዉ ሄደዋል፡፡ የሰዉ ልጆችን መተዳደሪያ የሆነዉን እና የሰዉ ልጅ እድሜዉን ሠዉቶ እና ተምሮ ያገኘዉን ስራ ሊቀሙት ከደጃፉ እያነፈነፉ ይገኛል፡፡ በአለም ላይ አሁን አሁን እጅግ ጥንቃቄ የሚጠይቁ ስራዎችን የነርቭ ቀዶ ህከምናዎችን ጭምር ሮቦቶች ያለምንም ስህተት ሲያጠናቅቁ እየተመለከትን ነዉ፡፡ ለሰዉ ልጅ የሚያዳግተዉን እና መቋቋም የማይችለዉን የዐየር ፀባይና አስቸጋሪ ስራ በሚያስደንቅ ሁኔታ እና እጅግ በፈጠነ መልኩ እያከናወኑ ይገኛሉ፡፡

          አሁን ከዓለም ጋር እኩል ለመራመድ ሁለት አማራጭ ነዉ ያለን የመጀመሪያዉ እና ዘላቂ መፍትሄ የሚሆነዉ ዜጎቻችን ከሮቦት እና ማሽኖ የበለጠ ብሩህ አእምሮ ያላቸዉ ናቸዉ እና አዕምሮአቸዉን በአግባቡ እንዲጠቀሙበት ማድረግ ሲሆን ሁለተኛዉ ደግሞ ያለ የሌለንን አቅማችንን ተጠቅመን አርቲፊሻል ኢንተሊጀንስ ቅንጦት ያለመሆኑን ተረድተን ትኩረት ሰጥተን ከኋላ መከተል፡፡ ይህ ካለሆነ ግን የሚመጣዉ ጊዜ እጅግ አስፈሪ እና ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ እጃችንን ተጠምዝዘን የምንረታበት ጊዜ መሆኑ አይቀሬ ነዉ፡፡


Reviews

Post Comment